የካቲት 3/2018 ዓ.ም
ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል
ደሴ
የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት ከሚባል ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከየካቲት 1 ቀን/2018 ዓ ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ያህል የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና እና ከዚሁ በተጓዳኝም ከካርተር ሴንተር ጋር በመሆን የዓይን ቆብ ፀጉር መቀልበስ ቀዶ ህክምና በነጻ እየሰጠ ሲሆን በዚህ የህክምና አገልግሎት እስከ አንድ ሽህ አምስት መቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
እንደሚታወቀው ሆስፒታሉ በመደበኛ ከሚሰጠው የዓይን ህክምና አገልግሎት በተጨማሪ በዘመናዊ ህክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በየዓመቱ እስከ ስምንት ሽህ ለሚሆኑ ታካሚዎች ለዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ ለእንባ ቱቦ መዘጋት እና ለዓይን ቆብ ፀጉር መቀልበስ ችግሮች ዘመቻ በማድረግና ነፃህክምና በመስጠት አበው “ልጅ ከጦረው ዓይን የጦረው” የሚሉትን ብሂል እውን በማድረግ ለበርካቶች የዓይን ብርሃናቸውን እየመለሰ ይገኛል ።
የዓይን ህክምና ዘመቻው በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ የሚከናወን ሲሆን ሆስፒታላችን ቀጥተኛ ከሆነው ህክምና ባሻገር በአካባቢው ለምግብና መጠጥ አቅራቢዎች ፣ ለአልባሳት ሽያጭ ወዘተ እንዲሁም ለህዝብ ማመላለሻ እና ታክሲ አሽከርካሪዎች የአጭር ጊዜ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።
ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል
ለበለጠ መረጃ ዌብ ሳይታችን ፡ ቴሌግራም እና የፌስ ቡክ ገጻችን ይጎብኙ እንዲሁም በ8352 በነጻ የስልክ ጥሪ መረጃ ያግኙ ።




